የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት በፈቃደ እግዚአብሔር በብፁዕ  አቡነ እንድርያስ አሳሳቢነት በገዳሙ  የተወሰኑ ዲያቆናት በጥቂት የአጥቢያው ወጣቶች  አማካኝነት በ1957 ዓ.ም. ተመሠረተ፡፡ “ዓምደ ሃይማኖት መንፈሳዊ  የወጣቶች ማኅበር” የሚል ሥያሜም ተሰጠው፡፡ በወቅቱ ወላጆችን አሳምኖ ወደ ቤተክርስቲያን ልጆቻቸውን እንዲያመጡ ለማድረግ ብርቱ ጥረት ተደርጓል፡፡ በተለይም የወቅቱ የገዳሙ አስተዳዳሪ የነበሩት የሰንበት ት/ቤቱ መሥራች መምህር ቀጸላ ሰይፈ ሥላሴ (በኋላ ብጹዕ አቡነ እንድርያስ) ለወላጆች (ለምእመናን) ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ ወላጆች ልጀቻቸውን ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት ያመጡ ጀመር፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቱ ሲመሠረት የነበሩት ጥቂት አባላት ቢሆኑም ከጊዜ ወደጊዜ የአባላቱ ቁጥር እየጨመረ መንፈሳዊ አገልግሎቱም እየሰፋ መጣ፡፡ የሃይማኖት ትምህርት ከመማራቸው በተጓዳኝም የመዝሙር፣ የልማትና የበጎ አድራጎት ሥራና ሥነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ይተገበሩ ጀመር፡፡ በዓበይት በዓላት በንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥት በመገኘት ጭምር በመገናኛ ብዙኀን በሚተላለፉ ዝግጅቶች ላይ የመዝሙር አገልግሎት ያቀርቡ ነበር፡፡ 

በተለይ በዚያን ዘመን ወጣት ሴቶች  መቋሚያ ተሸክመው፣ ጸናጽል ይዘው ሲዘምሩ የተመለከቱ ምእመናን እና ጥቂት አገልጋዮች ሥርዓት ተጣሰ፣ ሕግ ተፋለሰ ብለው እንግዳ በሆነባቸው ነገር ተደናግጠው ተቃውሞ ቢያቀርቡም በአባቶች የግንዛቤ ትምህርት  ተሰጥቷቸው አገልግሎቱ እንዲቀጥል ሆኗል፡፡  ለወጣቱ መጠንከርና በሥነምግባር መታነጽ የሰንበት ትምህርት ቤቱ መሥራች የነበሩት መምህር ቀጸላ ያበረከቱት አስተዋጽዎ እጅግ የላቀ ነበር፡፡ ትውልድ በሃይማኖት እንዲጸና፣ በምግባር እንዲጎለብትና ለሀገር ለወገን የሚጠቅም መልካም ዜጋ ሆኖ እንዲያድግ፤ በአበው  እግር ተተክቶ ቅድስት ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግል ሆኖ ይቀረጽ ዘንድ ከወጣቱ ጋር በጉባኤ በመታደም በቅርበት ሆኖ በመከታተልና ችግሮቻቸውን በመፍታት በመኀከላቸው ፍቅር እንዲሰፍን ያደርጉ ነበር፡፡